2015 ሜይ 31, እሑድ

ምን ችግር አለው?


. . . አሁን እስቲ ዝምብለው ሲያካብዱ ነው እንጂ ኢህአዲግ ይህን ሁሉ ሽርጉድ ብሎ ያዘጋጀውን ሰርግ ቢሞሸርበት ምን ችግር አለው?
ህዝቡ በነቂስም ሆነ በቀሚስ ወጥቶ ቢመርጥ ባይመርጥ ምን ችግር አለው? የአፍሪካ ህብረትን የሚያክል ግዙፍ ተቋም(በህንጻው እርዝማኔ ነው) ስራ አስፈትተን ታዘቡን ባንል ምን ችግር አለው? . . . ችግር የለውም . . .
አንዳንዶቻችንን እንደሆነ አይነት በሽታ የተጠናወቱን አንዳንዶቻችንን ደሞ ያማረሩን የዘመኑ አነጋገሮች ቢኖሩ “ምን ችግር አለው?” እና “ችግር የለውም!” ናቸው። የሚገርመኝ ነገር የመጀመሪያው ጥያቄያዊ ዓረፍተ ነገር ቢሆንም በተጠቃሚዎቹ ድምፀት እና መልስ አለመጠበቅ የተነሳ እንደጥያቄ ሲቀርብ አላስተውልም። ለ”ምን ችግር አለው?” እንደመልስ ባይቀርብም መልስ የሚመስለው “ችግር የለውም” በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው በቸልተኝነት፣ በመሰላቸት፣ በችኮላና መሰል መንገዶች ነው  -ለዛውም በጠያቂዎቹም ሳይቀር። አሉታዊ አጠቀቃቀሙ እና ተፅዕኖው እየጎላ መጣ እንጂ “ችግር የለውም!” የሚለውን አነጋገር መጠቀም እንኳን ችግር የለውም(አመለጠኝ)። ብዙዎቻችን የማናውቃት ጎረቤታችን ኬኒያን ጨምሮ የስዋሂሊ ተናጋሪዎች “ሃኩና ማታታ” የሚሏት እንደውም ከአፍሪካ ውጪ ሁላ ታዋቂ የሆነች ሃረግ አለቻቸው እዚም እዛም የሚጠቀሟት ትርጉሟ “ችግር የለም” ነገር ነው። አጠቃቀሙም በጣም አዎንታዊ ይላሉ - እኛ “ሁሉ ሰላም” እንደምንለው አይነትም ሊወሰድ ይችላል። የኛዋ ችግር የለውም ግን ጭራሽ አድማጩ ያላሰበውን ችግር ታሳስባለች። ችግር በሌለበት ችግር የለውም። ችግር በችግር(ፕሮብሌም) ተከበንም ችግር የለውም። እውነቱን ልንገራችሁና እኔ እንደውም ከዚህ በኋላ አንድ ሰው ሊያሳምነኝ “ችግር የለውም” ባለ ቁጥር ችግር ብቻ ሳይሆን አደጋ ነው የሚታየኝ - “አደጋ አለው” አለች አሉ ያቺ ሴትዮ።
ቆይ ግን እነዚህን አባባሎች በስፋት እየተጠቀምን መምጣታችን ችግር ምን ያህል እንደተተበተበብን ነው እሚያሳየው ወይስ ችግርን ምን ያህል ተቆጣጥረንና ቀለል አድርገን መመልከት ለመቻል መብቃታችንን? ይህን ጉዳይ የስነ-ችግር ባለሞያዎች ጥናት ቢያደርጉበት ችግር የለውም።
አንድን ነገር ለማድረግም ሆነ ላለማድረግ የግድ ችግር መኖር ወይም አለመኖር አለበት እንዴ ጎበዝ? እርግጥ ነው ችግር መፍትሔን ያመጣል፣ ችግር ብልሃትን ይፈጥራል ወዘተ ወዘተ... አንድ ነገር ልትሰራ ስትል “ቆይ በኋላ ብትሰራው ምን ችግር አለው?” ይልሃል ድራፍት ካልጋበዝኩህ የሚል ጓደኛህ። ምናልባትም ካንተ በላይ የተማረ ነውና ያሉትን ችግሮች ማስረዳቱ ስድብ መስሎ ይሰማህ ይሆናል። ወይም ደሞ ትርጉሙ ያንተ ግብዣ ቀረ አልቀረ ፣እንደውም ካንተጋር መጠጣት አይመቸኝም ምናምን ምናምን . . . ምናምን ይመስልህና አንተም “አንድ ሁለት ብጠጣ ችግር የለውም” ትለዋለህ እራስህን ከዛም እሱኑ - ያለውን ችግር ሁሉ ስታውቀው።
. . . ሴትዮዋ መንገድ ዳር ሚኒባስ ታክሲው ሁሉ ሞልቶ እየመጣ አልጭን ብሎ ሲያልፋቸው ቆይተው በመከራ የተገኘ አንድ ሚኒባስ ሳ አጠገባችው መጥቶ ገጭ “ጎሽ ልጄ ተባረክ አንተ ትሻላለህ” ብለው የጀመሩትን ምርቃት ሳይጨርሱ እንደ አነባበሮ አንዱ ባንዱ ላይ የተነባበረወን ተሳፋሪ አይተው መለስ ቢሉ ረዳት ሆዬ ጭራሽ እያዋከበ “ግቡ እንጂ ማዘር” ይላል “ምን ላይ ነው እምገባው?”
“ችግር የለውም ይጠጉሎታል”
“የት ነው ሚጠጉት? ተው ለኔ አይሆንም”
“ኧረ ችግር የለውም ማዘር ኑዚ” የዘረጋውን እጁን እንኳ ለማሳረፍ ያልበቃች ቦታ እየጠቆመ።
ሴትዮዋም አሉ “የዘንድሮ ልጆች ችግር የለውም ችግር የለውም እያላችሁ ነው ችግር ያመጣቹብን”
ኧረ ማዘሮችና ፋዘሮች ደሞ የዘንድሮ ልጅ ምናምን እያላችሁ አትንቆሩና እንዴ እኛ በስንቱ እንነቆር። ደሞስ ምን አርጉ ነው እሚሉን? መሞት እንኳን አልተፈቀደልንም እኮ። የደርግ ዘመን ወጣት ነጭ እና ቀይ ሽብር እየተፋፋመበት ይረሸን ነበር። የሚታገለውም ለውጥ ወይም ሞት በሚል አይነት መንፈስ እንደነበር የስሚ ስሚ ሰምተናል። እኛ ግን ቀለሙ ያልታወቀ ሽብር እየተፋፋመብን ድንዝዝ፣ ክልትው፣ ኩምሽሽ፣ ሁሉን እርስት፣ በአካልም በመንፈስም ካገር ሽሽት ብለን አለን። እናም አሁን ግርም እያለን እኛ የመረጥነው ነው እሚመራን እሱ የመረጠንን ነው እሚመራው? ተወካዮች ምንድነው? ምርጫ ምንድረነው? ባንመርጥ ምን ችግር አለው?(ባንመርጥ የሚለው ቃል ቢጠብቅ ባይጠብቅ ምን ችግር አለው?) ምናምን ልንል ይቃጣናል። ደሞ ብንልስ ምን ችግር አለው?



ሰላም!

2015 ሜይ 19, ማክሰኞ

ንቃት

ንቃት

ይህ ለማንቂያ ደውልነት የተዘጋጀ ጦማር ነው፡፡ እነሆ ነገር ሁሉ መልካም ሆኖ ይህ ጦማር ይፈጠር ዘንድ ተችሏል፡፡

ንቃት ንቃት ንቃት… ከምን?.... ካለንበት አውቆ የመተኛት አባዜ ነዋ፡፡ ምንም እንኳ አውቆ የተኛ ሲቀሰቅሱት ባይሰማም… ቆይ ቆይ ግን ማን የነቃ ሆኖ ማንን ሊቀሰቅስ ነው…? በዚ ከወሰድነውማ አኔም ነቄ እናንተም ነቄ፡፡ ነቄ ለ ነቄ አይደባለቄ እንበል ይሆን?

ሞቲቬሽን የሚሉትን ቃል መነቃቃት በሚል በብዙ ሰዎች ሲተረጎም ከማስተዋል ብሎም አዌክኒንግ የተሰኘው ጥልቅ ትርጉም ያለው የእንግሊዘኛ ቃል መንቃት ወይም ማንቃት በሚል በአቻነት ጥቅም ላይ ሲውል ከመታዘብ የተገኘ ስያሜ ነው፡፡
ይህም በእርግጥ የአማረኛችንን ጥንካሬ ለማሳየት የሚችል ይመስለኛል፡፡ ለዚህም እንደምክንያት የማቀርበው መበረታታትም ሆነ መነቃቃትን በአንድ ላይ አዝሎ ማሳየት የሚችል አቅም ያለው ቃል በመሆኑ ነው፡፡

...ወዳጆች እስኪ የሚያበረታታንን ሰውም ሆነ ሃሳብ በማጣት እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ሃገር ያጣናቸውን ነገሮች እናስብ… እልፍ አይሆኑምን? በተለይ እንደ ብርድልብስ የተከናነብነው መፋዘዝ የሞቀን፣ እንደ ፍራሽ የተኛንበት ቸለኝተኛነት እና እንደማክዳ የተንተራስነው ግለኝነት የተመቸን፣ እንደ መብራትም ያጠፋነው አስተዋይነት ያዘጋጀን፣ ወዘተ እና ወዘተ አይነት ሆኖ እንቅልፍ ብቻ የመረጥን መስሎ አይሰማችሁም?
…እስቲ እንቀሳቀስ መንቀሳቀሱንስ የተካንበት ይመስላል… ሃገር ውስጥ ተፍተፍ እውጪም ተፍተፍ… እንደውም በታሪካችን ከምንግዝውም በላይ በውስጥም በውጪ እየተንቀሳቀስን አይሆንም ብላችሁ ነው…

እናም ይህ ጥሪ በንቃት እንንቀሳቀስ ዘንድ እንድንቀሳቀስ ነው! … ተንጠራራን ማለት ነው… 
ለንቃት…፡፡

ሰላም!