2020 ጁላይ 27, ሰኞ

እኔና ግድቡ

. . . ‘ግድቡ የኔ ነው’ የሚል አቋም ይዤ አላውቅም. . . ‘ብላክ ላይቭስ ማተርስ’ም አላልኩም። የግድቡና የጥቁር ህይወት ጉዳይ የሚገናኝ ቢሆንም እንደነዚህ አይነት ባለመንሰላል ቃላት (ሃሽታግ) ብዙም አልጠቀመም - የጅምላ አስተሳሰብ ውስጥ የሚዘፍቁኝ ይመስለኛል - ሃሽታጋም መሆን አልፈልግም። እንደዚህ ብልም ግን ግድቡ ላይ አያገባኝም ማለት አይደለም እንደውም በዚህ ግድብ የተነሳ የደረሰብኝን ላጋራችሁ ነው የተነሳሁት። እስከዛሬ ለምን እንዳልጻፍኩት ለራሴም ግራ ነው።

የዛሬ ዓመት ከምናምን ለስራ ጉዳይ ለመጀምሪያ ጊዜ ከሃገር ወጣሁ። በገዛ የሃገሬ አየር መንገድ አውሮፕላንና በገዛ የሃገሬ ቆነጃጅት የበረራ አስተናጋጆች ቀለም አልባ ቆዳ ያላቸው ሰዎች /ነጮች/ በሁሉም ነገር ቅድሚያ ሲሰጣቸው ሳይና ባረፍኩበት ሆቴል ውስጥ ሊፍት ስሳፈር ያጋጠሙኝ ሰዎች አንዳች ዘራፊ እንደገጠማቸው አይነት ነገር ሲጨማቀቁ ሳይ - ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁርነት ተሰማኝ፣ አሃ ለካ ጥቁር ነኝ አልኩኝ፣ ሬሲስት ሃገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ለካ የዕለት ተዕለት ኑሮዋቸው እንዲህ ነው አልኩ. . . ጠቆርኩ። ይኼኔ እኮ እነዛ የበረራ አስተናጋጆችም ‘ብላይክ ላይቭስ ምናምን’ ብለው ለጥፈዋል - ቲሽ!

ጦሰኛው ግድብ ጋር ከመድረሴ በፊት ላንድ ሎክድ አገር ውስጥ የመኖር አንዱን መዘዝ ላውጋችሁ። ከውቅያኖስ ወይም ከባህር የራቀ ህዝብ በዛ ውስጥ የሚገኙትን እንስሳት ከመብላትም በእጅጉ ይርቃል። እኔም እንደአብዛኛው የባህር በር አልባ አገር ሰው ከባህር ለሚገኙ ምግቦች እንግዳ በመሆኔ ‘ሽሪምፕ’ የሚባል ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ቀመስኩ።

ወደ ሆቴሌ እንዲያደርሰኝ የተመደበው መኪና አርፍዶ በመምጣቱ ‘ይኼ ሰውዬ ሐበሻ ነው ወይም ሌላ አይነት ጥቁር መሆን አለበት’ እያልኩኝ እያለ የሆነ ኮርስ ያስተማረንን ህንዳዊ የመሰለ ሰው ከች አለና ‘ሚስተር ተማም’ አለኝ በቲፒካል የህንድ አክሰንት። እኔም እንደጥቁር ራሴን አሳንሼ እንደነበር የገባኝ ሻንጣዬን ተቀብሎ መኪናው ላይ ለመጫን ሲል አይሆንም ብዬ ስግደረደር ነበር። የካምፓኒው ፕሮቶኮል ስለሆነ የእሱ ስራ እንደሆነ ሲነግረኝ ነው ራሴን ቆንጠጥ አድርጌ ደረቴንም ነፋ አድርጌ ሻንጣዬን የሰጠሁት። አጅሬ የማርፍበትን ማርዮት ሆቴልም በትክክል ለማወቅ ተቸግሮ ሲያሸከረክረኝ ቆየ። እኔ ከሱ ተሻልኩና ሃምዳን ቢን ሞሐመድ ስትሪትን በካርታ ላይ አገኘሁት። ሰው እየጠያየቀም ቢሆን መድረስ ከነበረብኝ ሰዓት አስረፍዶ አደረሰኝ።

ክፍሌን ተረክቤና ተሽሞንሙኜ የሄድኩበትን ጉዳይ እራሴን በማስተዋወቅ ‘ሀ’ ብዬ ልጀምር ተዘጋጀው። ከሰላሳ ምናምን ሃገራት የመጡ የተለያዩ ሰዎች ያሉበት አቀባበል እየተጠናቀቀ እንደኔው ያረፈዱ ሁለት ሰዎች እራሳቸውን እያስተዋወቁ ደረስኩና ወዲያው እኔም ስሜን ከሃገሬ ጋር አድርጌ መጥራቴ የፈጠረብኝን ልዩ ስሜት እያጣጣምኩ እራሴን አስተዋወቅኩ። ከካራ ወጥቼ ኡራኤል አካባቢ መኖር ስጀምር ራሴን የካራም የኡራኤልም ልጅ ነኝ አልልም ነበር፣ ጅማ ዩንቨርሲቲ የተመደብን ጊዜ ይመስለኛል አዲስ አበባ የሚለውን ቃል መጠቀም የጀመርኩት . . . አንድ ቦታ ብዙ ጊዜ ስንሆን በቃ ነገር ዓለሙ ሁሉ ያ ቦታ ብቻ አይነት ነገር ይሆንብን የለ?! እኔም ከኢትዮጵያ የምትለዋን ባገኘኋት አጋጣሚ ሁሉ በኩራት ከማለቴ የተነሳ በመጣበት ሃገር ስም ስጠራ የነበርኩት እኔ ብቻ ሳልሆን አልቀርም።

ትውውቁ እንዳለቀ ከዛ ሁሉ ነጭ መሃል የነበሩት እናቴን የሚያካክሉና አክስቶቼን የሚመሳስሉ ሶስት ጥቁር ሴቶች አንድ ላይ ፎቶ መነሳት ጀመሩ እኔም ምን እንደጠራኝ አላውቅም አራተኛ ሄጄ ልጥፍ አልኩኝ። የሴኔጋል፣ የጋና እና የትሪኔዳድ ተወካዬች ነበሩ - እኔም ብቸኛው ጥቁር ወንድ ነበርኩ። ያቺ የበረራ አስተናጋጅ የስራዋን ይስጣትና (የሚያበር ያብርራት፣ የሚያስተናግድ ያስተናግዳትና) የረባ ምግብ እንዳላገኝ ለኔ ዋናውን ምግብ ሳታቀርብ ነጩን ሼባ መጠጥ ካልጋበዝኩህ የሚመስል ጥያቄ ስታቀርብለት ሳይ ዘጋኝ በቅጡ አልበላሁም ነበርና ሪሴፕሽኑ ላይ ከነበረው ምግብ አይቼ የማላውቀውን መርጬ ማጫወት ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ የባሩ ባንኮኒ ላይ ተፈናጥጬ ምግቤን በወይን እያወረድኩ ከኒውዮርክ ከመጣች ሴትዮ ጋር የጦፈ ወሬ ውስጥ ገባሁ። በመሃል አንገቴና ጉንጬ ዙሪያ የሚያሳክክ ነገር ያሸማቅቀኝ ጀመር። ‘ታጥቤ ልብስ ቀይሬ ነው የወጣሁት።’ ‘ሳሙናው አልተስማማኝም ይሆን?’ ‘ኸረ እዚህ አገር አይታከክም!’ ‘ከአንድ ብርጭቆ በላይ አልጠጣሁ. . . ደሞ ወይን ያሳክካል እንዴ?. . . ለዛውም የዚህ ሃገር?!’

በጠዋት ተገናኝተን ቁርስ አንድላይ በልተን በባስ እንደምንወሰድ ተነገረንና ሁሉም እረፍት ሊያደርግ ወደየ ክፍሉ ሲገባ እኔም ለጓደኞቼ ያለሁበትን እያሳየሁ ላቅራራ ዋይፋይ እየፈለግኩ እያለ አየር አጠረኝ፣ ሳል በሳል ሆንኩኝ፣ ሰውነቴን የሚያሳክከኝ ነገር እየባሰ መጣ (ያኔ ኮቪድ ቢኖር መቶ በመቶ እሱ ነው ነበር የምለው). . . ብቻ ማሳል፣ ብቻ ማከክ፣ ብቻ አይን መብላት. . .  የምሆነው ነገር አሳጣኝ ይባስ ብሎ ከፍተኛ ቁርጠት። ሆድ ቁርጠት ለአፍሪካዊ ብርቅ አይሆንም እንደዚህ ግን ስለት የመሰለ ቁርጠት ገጥሞኝ አያውቅም።

ወደ ክፍሌ ስበር ሄድኩኝ። መስታወቱ ውስጥ ያለሁት እኔ መሆኔን ለማመን ያስቸግራል። በብዙ ነገሮች ቀልቶ የሚያውቀው አይኔ ነጩም ነጭነት ጥቁሩም ጥቁርነት የመረራቸው ይመስል እንዲህ ቀልተው ግን አያውቁም (ሬድ ላይቭስ ማተር ብለው ነበር)… 

. . . ይቀጥላል . . .