2016 ኤፕሪል 11, ሰኞ

ንጹህ አቅም


ሰላም ወዳጆች
ይህች ጦማር ታዳሚዎችዋን ለማንቃት ተናስታ እራሷ ተኝታ ብትከርምም ከአሁን በኋላ በተከታታይ ከ ዲፓክ ቾፕራና ሌሎች ጸሃፍት በሚቀነጨቡ ጽሁፎች ልንቀሰቅሳት ወደናል። በማህበራዊ ገጥ የቀረበ የመጀመሪያ ትርጉም ስራዬ ነውና ማንኛውንም አይነት አስተያየት ከአንባቢ ለመቀበል በጉጉት እጠብቃለሁ - በተለይ ደግሞ ስራዎቹን ቀድመው አንብበው ከነበሩ ታዳሚያን። ቅድሚያ ጦማሯን እንቀስቅስ ከዛም እራሳችንን... መቀሳቀስም አይደል አላማችን?። የመጀመሪያዋን ማንቂያ እንኋት ‘ ንጹህ አቅም’! እዚህ ጋር ንጹህ ስንል የምንጠቀምበት ቃል ተፈጥሯዊ ንጽህናን በዓለማዊ አኗኗር ያልበለዘ ቅድስናን ለማመላከት ሲሆን የሰው እውነተኛ ማንነት ላይ የሚቀርቡ ሃሳቦችን ከሐይማኖቶች ጋር በማይጣሉ መልኩ ሳይሆን ሁሉም ሐይማኖተኛ ሰው ከየራሱ ሐይማኖት አስተሳሰብ አንጻር ሊያየው በሚችለውመልኩ የሚቀርቡ ይሆናሉ። በዚህም አቀራረብ ዙሪያ የማስከፋው ምንም አይነት አካል የሚኖር እንደሆን አለመከፋትን መምረጥ የዛ አካል ድርሻ መሆኑን በማመላከት አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

ንጹህ አቅም

 ዲፓክ ቾፕራ


የመጀመሪያው የስኬት መርህ ‘the law of pure potentiality’ ወይም እዚህ እንደምንጠቀምበት ትርጉም የንጹህ አቅም መርህ ነው። ይህ መርህ የተመሰረተው እኛ ሰዎች በመሰረታዊው መገኛችን ማንነታችንንጹህ ንቃት የመሆናችን ሃቅ ላይ ነው። ንጹህ ንቃት ደሞ ንጹህ ብቃት ወይም አቅም ነው ይህም የአማራጮች እና ማለቂያ የሌለው የፈጠራ ችሎታ መገኛ መስክ ነው። ንጹህ ንቃት የመንፈሳዊ ማንነታችን መገለጫ ከመሆኑም ውጭ ማለቂያ የሌለውና ያልታሰረ ንጹህ ደስታም ነው። ንጹህ እውቀት' ገደብ የለሽ ፀጥታ' አይበገሬነት' ጥራትና ሃሴት የንጹህ ንቃት መለያዎች ናቸው። ይህም የሰው ልጆች መሰረታዊ ተፈጥሮ ወይም ማንነት ነው።
ሰው መሰረታዊ ተፈጥሮውን ወይም እውነተኛ ማንነቱን ሲያውቅ ያ ዕውቀት በራሱ ማንኛውንም ህልሙን ማሳካት የሚያስችል አቅም ይሆናል ምክኒያቱም ሰው ያለ የነበረና የሚኖረው ዘላለማዊ ችሮታና ገደብ የለሽ አቅም ነው። የንጹህ አቅም መርህ ያልነው እንግዲህ የአንድነት መርህም ሊባል ይችላል ምክኒያቱም ህልቆ መሳፍርት ከሌለው ተፈጥሮ ላይ ከሚስተዋለው ልዩነት በስተጀርባ ያለው የመንፈስ አንድነት ነውና። በሰውልጅ እና በዚህ የሃይል መስክ መካከልም ምንም የሚለያይ ነገር የለም። ሰው እውነተኛ ተፈጥሯዊ ማንነቱን ባገኘ ቁጥር ወደ ንጹህ ብቃት ወይም አቅም እየተጠጋ ይሄዳል።
ራስን መሆን ‘self-referral’ ማለትውስጣዊ  የማነጻጸሪያ ነጥባችንን ከራሳችን መንፈስ ውጭ ባሉ ነገሮች ሳይሆን መንፈሳችን ላይ ማድረግ ማለት ነው። የዚህም ተቃራኒ ነገሮችን ማንጸሪያ ማድረግ ‘object-referral’ ሲሆን በዚህም ምንግዜም ከኛ ውጭ ባሉ እንደ ሁኔታዎች' ምህዳሮች'ሌሎች ሰዎችእንዲሁም በነገሮች ተጽእኖ ስር እንውድቃለን። ነገሮችን ማንጸሪያ በምናደርግበት ጊዜ የሌሎችን እውቅናና ይሁንታ ያለማቋረጥ እንፈልጋለን፤አስተሳሰባችንና ባህሪያችንም መልስ በመፈለግ ላይ የተጠመደ መሆኑ ይህን መንገድ ፍርሃት ላይ የተመሰረተ ያደርገዋል።
ነገሮችን ማንጸሪያ በምናደርግበትጊዜ ነገሮችን ለመቆጣጠርም አስገዳጅ ፍላጎት ይሰማናል። ይህ አስገዳጅ ፍላጎት ውጫዊ የሆነ ሃይልን ለማግኘት የሚሰማን ሲሆን  እውቅናን ወይም ይሁንታን ለማግኘት' ነገሮችን በቁጥጥራችን ስር ለማድረግ እንዲሁም  ውጫዊ ሃይልን ለማግኘት የሚሰሙን አስገዳጅ ፍላጎቶች ሁሉ ፍርሃት ላይ የተመሰረቱ ይሆናሉ። የዚህ አይነቱ ሃይል ንጹህ አቅም ወይም እራስን የመሆን ሃይል አይደለም ጭራሹንም እውነተኛ ሃይል  አይደለም። እራስን የመሆንን ሃይል ስናራምድ ፍርሃት ይጠፋል' መቆጣጠር የምንፈልገው ነገር አይኖርም' የማንንም የምንንም እውቅናም ሆነ ይሁንታ ወይም ውጫዊ ሃይል ለማግኘት  አንታገልም።
ነገሮች ማንጸሪያ ሲሆኑ ውስጣዊ ማንጸሪያ ነጥባችን ኢጎ ብለን የምንጠራው ሃሰተኛው ማንነታችን ነው። ኢጎ የራስ ምስል ነው፤ ማህበራዊ ጭምብል ነው፤ የምንጫወተው ሚና ነው። ማህበራዊ ጭምብላችን ሁሌም ይሁንታና እውቅናን እንዲሁም መቆጣጠርን የሚፈልግ ሲሆን በፍርሃት የሚኖር በመሆኑም የሚያቆየውን ሃይል የሚፈልግ ነው።
እውነተኛው ማንነታችን ሙሉለሙሉ ከነዚህ ነገሮች የጠራ ሲሆን በሂስ የማይኮስስ' በፈተና የማይሸበር እና ከማንም የበታችነት የማይሰማው እንደውም ሁሉም ሰው በመሰረቱ አንድ መሆኑን፤ በተለያየ ሰውነት ውስጥ ያለ አንድአይነት መንፈስ መሆኑን ስለሚረዳ በአጉል ኩራት ሳይያዝ ከማንም የበላይነት አይሰማውም።
ነገሮችን ማንጸሪያ በማድረግና እራስን ማንጸሪያ በማድረግ መሃል ያለው መሰረታዊ ልዩነት ይህ ነው። እራሳችንን ማንጸሪያ ስናደርግ በፈተና የማይበረግገውን' ሁሉንም ሰው የሚያከብረውንና ከማንም የበታችነት የማይሰማውን እውነተኛውን ማንነታችንን እናገኛለን። እራስን የማወቅ ሃይል ትክክለኛው ሃይል ነውና።
በሌላኛው በኩል በነገሮች ማንጸሪያነት የተመሰረተ ሃይል የውሸት ሃይል ነው። ኢጎ ወይም ሃሰተኛው ማንነታችን ላይ የተመሰረተ በመሆኑም  የሚቆየው የምናነጻጽርበት ነገር እስካለ ድረስ ብቻ ነው። ማዕረግ ያለው ሰው ቢሆን' የሃገር ፕሬዝዳንትም ሆነ የተቋም የበላይ ኅላፊ ወይም ብዙ ገንዘብ ያለው ባለጠጋ የሚደሰትበት ሃይል ከማዕረጉ' ከስራው ወይም ከገንዘቡጋር አብሮ ጠፊ ነው። ኢጎ ላይ የተመሰረተ ሃይል እነዚህ ነገሮች እስካሉ ድረስ ብቻ የሚቆይ ነው። ማዕረጉ' ስራው ወይም ገንዘቡ በጠፉ ጊዜ የሚጠፋ ሃይል ነው።
ራስን በመሆን የሚመጣው ሃይል የራስ ሃይል ግን እራስን ከማወቅ የሚመነጭ በመሆኑ ቋሚ ነው። ይህም የራስ ሃይል ያልነው የሚከተሉት መገለጫ ባህሪያት አሉት። ሰዎችን' የምንፈልጋቸውን ነገሮችንና  ሁኔታዎችን ሁሉ ወደኛ ይስባል። ይህም በክብር ከመገለጥ የሚመጣ መለኮታዊ ድጋፍ በመሆኑ የተፈጥሮ ህግ ድጋፍ ተብሎም ይጠራል። ሃይላችንም ከሰዎች ጋር በመጣመራችን የምናጣጥመው ሰዎችም ከኛ ጋር በመጣመራቸው የሚያጣጥሙት አይነት ነው። ሃይላችን የጥምረት ነው፤ ይህም ጥምረት ከፍቅር የመጣ ነው።

ይቀጥላል ...

ሰይፈ ተማም 2008